Channel Avatar

Sheger FM 102.1 Radio @UC9uvm3QhajePOVdct3Jv8Hg@youtube.com

484K subscribers - no pronouns :c

#ShegerFM #Ethiopia #ሸገርኤፍኤም102.1 Sheger FM 102.1 'Yenanet


Welcoem to posts!!

in the future - u will be able to do some more stuff here,,,!! like pat catgirl- i mean um yeah... for now u can only see others's posts :c

Sheger FM 102.1 Radio
Posted 4 days ago

#ታሪክን_የኋሊት

ነሐሴ 16 2017

በከፍተኛ ጥንቃቄ ከተቀመጠችበት ሙዚየም የተሰረቀችው የሞናሊዛ ሥዕል የተገኘችው በ1903 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡

ሊዮናርዶ ዳቬንቺ፣ የሳላትና በዓለም ዙሪያ ዝና ያተረፈችው ሞናሊዛ ፣ የተሰረቀችው ፓሪስ ከሚገኘው የሉቨር ሙዚየም ነው፡፡

የሞናሊዛ መጥፋት፣ መላ ፈረንሳይን በጥፍር የሚያስቆም ድንጋጤ ፈጠረባት፡፡
ሁለት አመታት የት እንደገባች ሳይደረስበት ቆየ፡፡

አንዳንዶች፣ ፈረንሳይን ለማዋረድ ጀርመኖች እንደሰረቋት ገመቱ፡፡
ሌሎች የስርቆት ልምድ ያለው ሌባ አልሰረቃትም ፣ ምክንያቱም ልምድ ያለው ሌባ ሞናሊዛን መስረቅ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ስለሚያውቅ፣ አይደፍርም የሚል ግምት ሰጡ፡፡
የምርመራ ሙያና ልምድ ያላቸው መርማሪዎች ሌት ተቀን ተከታተሉ፡፡

ግን ለሁለት አመታት አንዳችም ፍንጭ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

በኋላ እንደተረጋገጠው፣ ሞናሊዛን የሰረቃት ኢጣሊያዊው ቪንስንዝ ፔሩጋ ነበር፡፡
የደበቀበትንም ቦታ የተናገረው ራሱ እንጂ ታውቆበት አልነበረም፡፡
ፔሩጋ ቀደም ብሎ በሉቨር ሙዚየም በተቀጠረበት ወቅት የሞናሊዛ ሥዕል ያለበትን ሳጥን አከፋፈቱን ያውቃል፡፡

በሙዚየሙ ምድብ ስራው፣ ስዕሎችን ማፅዳት ፣ ሳጥናቸውን መጠገን ነበር፡፡
በሰረቀበት እለት፣ ሰራተኞች ከመግባታቸው ቀደም ብሎ የሰራተኞቹን ልብስ ለብሶ ትኩረት ሳይስብ ወደ ሞናሊዛ ተጠጋ፡፡

ስዕሉን ከሳጥኑ ውስጥ አውጥቶ ፣ በለበሰው ረጅም ቀሚስ ያዘ፡፡
ሰጥኑን እዚያው ካሉ የጀማሪዎች ስዕሎች ጋር ተወው፡፡
ሞናሊዛን በሚተኛበት ክፍል ደበቃት፡፡

ለመስረቅ ምክንያት ያደረገው፣ በኢጣሊያዊነቷ፣ በአርበኛነት ስሜት ነው፡፡
በእርሱ እምነት ፣ሞናሊዛ የኢጣሊያው ሰዓሊ፣ የሎናርዶ ዳቬንቺ ሥዕል ብትሆንም የፈረንሳዩ ንጉሥ ናፖሊዎን ዘርፎ መውሰዱና በባለቤትነት የያዘችው ፈረንሳይ መሆኗን በመቃወም መሆኑ ተናገረ፡፡

ከሁለት አመታት በኋላ የስዕል ስራዎችን የሚሰበስበው አልፈርዶ ጌሪ ደብዳቤው ደረሰው፡፡
ደብዳቤው “ሊዩናርዶ” በሚል ስም የተፃፈ ሲሆን፣ ሞናሊዛ ፍሎሬንስ የምትገኝ መሆኗን የጠየቀው ገንዘብ ከተሰጠው እንደሚመልስ ያትታል፡፡

ፈረንሳዮች በፍጥነት ገንዘቡን አቀረቡ፡፡

“ሊዩናርዶ” በሚል ስም የፃፈው ሰው ፣ ገንዘቡን ለመቀበል እቀጠረበት ቦታ ሲደርስ ተያዘ፡፡
ሊዮናርዶ የተባለው ፔሩጋ ሆኖ ተገኘ፡፡

ሞናሊዛ በነበረችበት ሁኔታ በመገኘቱ ደስታ ሆነ፡፡

ወደ ቀድሞው ቦታዋ ሉቨር ሙዚየም ተመልሳ፣ እስካሁን በጥንቃቄ ተይዛለች፡፡ ሞናሊዛ በቴክኖሎጂ የታገዘ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግላታል፡፡

ከ60 አመት በፊት ጀምሮ የ100 ሚሊዮን ዶላር ኢንሹራንስ ተገብቶላታል፡፡ በአሁኑ ምንዛሬ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡

ፔሩጋ የሰረቀበት ምክንያት ለሃገሩ ተቆርቆሩ መሆኑ ግምት ውስጥ ገብቶለት አንድ አመት እስራት ተፈርዶበት በሰባት ወራት እስራት ተለቀቀ፡፡

ሞናሊዛ ከተሰረቀችበት ከተገኘች 114 አመት ሆነ፡፡

https://youtu.be/hppcHF5dPhQ

202 - 0

Sheger FM 102.1 Radio
Posted 6 days ago

ታሪክን የኋሊት


ነሐሴ 14 2017


የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕክምና ከሚያደርጉበት ብራስልስ ማረፋቸው በመገናኛ ብዙሃን የተነገረው ነሐሴ 14/2004 ዓ/ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣናቸው ላይ እንዳሉ ለመሞት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ፣ በትጥቅ ትግል የመንግስትነት ስልጣን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ሊቀመንበር በመሆናቸው የሃገሪቱ መሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ቆይቶ በሕገ - መንግስቱ በተሰጠው ድንጋጌ መሰረት ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው፣ ለ21 አመታት ኢትዮጵያን መርተዋል፡፡
በትግራይ አድዋ ከተማ የተወለዱት ፣ አቶ መለስ ፣ ወደ ሕወሓት የተቀላቀሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ነበር፡፡
አቶ መለስ ፣ በስልጣን የቆዩበት ጊዜ ፣ በተለይ የምጣኔ ሐብቱ እድገት አለም አቀፍ ድርጅቶች እንዳረጋገጡት በሁለት አሃዝ ከፍ ያለበት ጊዜ ነው፡፡

በተለያዩ ክልሎችና በከተሞች ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የተመዘገበበትም ጊዜ ሆኗል፡፡
የህዳሴ ግድብንም በራስ አቅም እንዲገነባ ስራውን እንዲጀመር አድርገዋል፡፡
በአለም አቀፍ የመሪዎች ጉባኤ ተደማጭነት አግኝተው ፣ ኢትዮጵያ በበለፀጉ ሃገሮች ጉባኤ እንድትሳተፍ አድርገዋታል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ዋና ፅህፈት ቤት ከአዲስ አበባ እንዲነሳ የተደረገውን፣ ሙከራ ተከራክረው ማስቀረታቸው በበጎ ይታወስላቸዋል፡፡
በሌላ በኩል በርሳቸው የስልጣን አመታት በየክልሎቹ እኩል ተጠቃሚነት የሌለበት ፣ አድሏዊ አሰራር እንዲሰፍን ፣ እስርና አፈና በዝቶ የዜጎች የመብት ጥያቄ በሃይል እንዲጨፈለቅና መብታቸው እንዲጣስ ፣ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲጠራጠሩ ፣ የጥላቻ ቅስቀሳዎች እንዲስፋፋ አድርገዋል እየተባሉ በተቃዋሚዎቻቸው ይወቀሳሉ፡፡
በተለይ ከ1993 ዓ/ም የሕወሃት መከፋፈል ወዲህ ስልጣኑን ሁሉ በእጃቸው አድርገው የአንድ ሰው ፍላጎት የሚፈፅምባት ሃገር አድርጋዋታል እየተባሉ ይተቻሉ፡፡
***********
አቶ መለስ ዜናዊ በፕሬዝዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለ21 ዓመታት ከመሩ በኋላ በ57 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡
የቀብራቸው ሥነ-ሥርዓት ከ15 ቀናት በኋላ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካረፉ ዛሬ 13 ዓመት ሆነ፡፡


እሸቴ አሰፋ

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

📌 Telegram; t.me/ShegerFMRadio102_1

📌 YouTube: shorturl.at/P4mpX

📌 WhatsApp: tinyurl.com/ycxjmm3s

282 - 40

Sheger FM 102.1 Radio
Posted 1 week ago

መልካም የቡሄ በዓል!
የእናንተው ሬድዮ!
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: tinyurl.com/ycxjmm3s

362 - 7

Sheger FM 102.1 Radio
Posted 1 week ago

ታሪክን የኋሊት

ነሐሴ 12 2017

በሃገር አስተዳደር ፣ ከውጭ ወራሪዎችን በመዋጋት ፣ ከፍ ያለ ያመራር ተሳትፎ እንዳላቸው ታሪክ የመዘገበላቸው እቴጌ ጣይቱ የተወለዱት በ1832 ዓ.ም በዛሬዋ እለት ነበር፡፡

እቴጌ ጣይቱ ብጡል ወሎ የጁ አካባቢ ተወለዱ፡፡

በጊዜው የነበረውንና ለሴቶች ደረጃ የሚፈቀደውን፣ የመፃፍና የማንበብ ትምህርት ተምረዋል፡፡

ወይዘሮ ጣይቱ፣ አራተኛቸው የሆኑትን ባላቸውን ዳግማዊ አፄ ምንይልክን ካገቡ በኋላ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሚታወቁ ሆነዋል፡፡

እንደርሳቸው ሁሉ ነሐሴ 12 የተወለዱትንና በእድሜ በአራት አመታት የሚበልጧቸውን አፄ ምንሊክን ካገቡ፣ በኋላ የእቴጌነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ፣ የራሳቸው የታጠቀ ሰራዊት እየመሩ፣ ሌላ ጊዜም ወታደሮቻቸውን በአጋዥነት እየላኩ ፣በዘመቻዎች ላይ የሚሳተፉ ነበሩ፡፡

አዲስ አበባን ለከተማነት የቆረቆሩዋት ስያሜዋንም ያወጡላት እቴጌ ጣይቱ ናቸው፡፡

ቤቶች ለመስራት ፣ ደኑ ሲመነጠር አይተዋት የማያወቋት አበባ በማየታቸው ፣ አዲሷን ከተማ ፣ አዲስ አበባ ብለው ሰይመዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ብጡል ፣ በውጭ ፀሃፊዎች ጭምር በአድናቆት የተፃፈላቸው፣ የኢጣሊያን ወራሪ ሀይል ለመቋቋም ከዝግጅቱ እስከ ጦርነቱ ያሳዩት ተጋድሎ ነው፡፡

አፄ ምኒልክ፣ የውጫሌን ውል ማፍረሳቸውን ሲያስታውቁ፣ ከኢጣሊያው ተወካይ ጋር በተደረገው ንግግር ተሳታፊ ሆነው ቁርጠኛ አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡

ተወካዩ፣ ወረቀቱን ቀዶ ሲወጣ፣ ከት ከት ብለው ስቀው፣ “ጦርነቱን ነገ አድርገው ፤ ለዚህ የሚደነግጥልህ የለም” ማለታቸው ይጠቀስላቸዋል፡፡

በአድዋ ጦርነት ዘመቻ፣ እስከ 3,000 የሚደርሱትን የራሳቸውን ወታደሮች ይዘው ዘምተዋል፡፡

የኢጣሊኖች የመቀሌ ምሽግ የተሰበረው በእቴጌ ጣይቱ የጦር እቅድ ነበር፡፡

ተጠናክሮ የተሰራውን የመቀሌ ምሽግ፣ ፊት ለፊት ለመደምሰስ ባለመቻሉ እቴጌ ጣይቱን በቅድሚያ ቦታውን አስጠኑ፡

ኢጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን ውሃ መያዝ ይቻል እንደሆነ አሰለሉ፡፡


በግንባር ለሚዋጉት ሊቀመኳስ አባተ አማከሩ፡፡


ወደርምጃ ለመግባት የሚቻል መሆኑን ሲያምኑ ፣ እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ አፄ ምኒልክን አስፈቀዱ፡፡

እንዳቀዱት፣ 900 የሚሆኑ የራሳቸውን ወታደሮች ልከው ፣ ኢጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን የምንጭ ውሃ አስደፈኑ፡፡

ለ15 ቀናትም፣ በተደረገ ጥበቃ፣ ኢጣሊያኖች በውሃ ጥም ተጨንቀው ምሽጉን ለቀቁ፡፡
እቴጌ ጣይቱ በብዙዎች ዘንድ የማይታወቀውን ቼዝ መጫወት ፣ በገና መደርደር ይችላሉ፡፡ ብስክሌት መንዳትም ተለማምደው እንደነበረ ተፅፏል፡፡

አፄ ምኒልክ በሕመም ምክንያት እቤት ሲውሉ፣ የመንግስትን ስልጣን ወስደው በማንኛውም ጉዳይ መወሰንና ሹም ሽር ማድረግ ጀምረው ነበር፡፡

ግን ብዙም ሳይቆዩ ፣ የጊዜው ሹማምንት ፣ የመንግስቱ ስልጣን አፄ ምኒልክ እንዳዘዙት በልጅ ኢያሱና በእንደራሴው እንዲከናወን ፣ እርሳቸው ከስልጣን እርቀው ባላቸውን እንዲያስታምሙ ወሰኑባቸው፡፡

ከዳግማዊ ምኒልክ ሞት በኋላ፣ ከቤተ መንግስት ወጥተው እንጦጦ ሲኖሩ በተፈጥሮ ሕመም በ78 አመታቸው አርፈዋል፡፡

ቀብራቸው በጊዜው እንጦጦ ማርያም ቢፈፀምም፣ በኋላ ንግስት ዘውዲቱ ከባለቤታቸው አፄ ምኒልክ አፅም ጋር ፣ በበዓታ ለማርያም ገዳም አፅማቸው እንዲያርፍ አድርገዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ከተወለዱ 185 ዓመት ሆነ፡፡

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

📌 Telegram; t.me/ShegerFMRadio102_1

📌 YouTube: shorturl.at/P4mpX

📌 WhatsApp: tinyurl.com/ycxjmm3s

537 - 7

Sheger FM 102.1 Radio
Posted 2 weeks ago

ታሪክን የኋሊት



ሐምሌ 30 2017



አሜሪካ መቶ ሺዎችን የጨረሰውን አቶሚክ ቦንብ በጃፓኗ ሂሮሽማ ላይ የጣለችው በ1937 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡



አቶሚክ ቦምቡን በጣለችበት ያኑ እለት ከ150 ሺህ ሰዎች በላይ በአልተለመደና በአሰቃቂ አሟሟት ወደትቢያነት ተለወጡ፡፡

በአቶሚክ ቦንቡ ሰበብ ቆስለውና ተጠቅተው የነበሩ 60 ሺህ ሰዎች በሚቀጥሉት 5 ወራት ረገፉ፡፡

35 ሺህ ያህል ቆስለው በፅኑ ደዌ ተጠቁ፡፡

የአቶሚኩ ጨረር ተጠቂ የሆኑትና ሰውነታቸው ያገኛቸው፣ በሚቀጥሉት 50 አመታት ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ዳርጓቸው ተሰቃይተው ኖረዋል፡፡

ከ1930ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ፣ አሜሪካ በከፍተኛ ሚስጢር የአቶሚክ ቦምብ ስትሰራ ቆየች፡፡

የተሳካ ሙከራ ካደረገች በኋላ ፣በጃፓን ላይ እንዲጣል የወቅቱ ፕሬዘዳንት ሃሪይ ትሩማን አዘዙ፡፡

አሜሪካ ጃፓን ላይ አቶሚክ ቦምብ በጣለችበት ወቅት፣ ጀርመን ተሸንፋ በአውሮፓ ያለው የሁለተኛው የአለም ጦርነት፣ አብቅቶ ነበር፡፡

ጃፓን ግን፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ ጦርነቱን ቀጠለች፡፡

አሜሪካ፣ ጃፓንን በእግረኛና በአየር ሀይሏ ለመውረር ብትፈልግ፣ ከፍተኛ እልቂት እንደሚጠብቃት፣ የፕሬዘዳንት ትሩማን አማካሪዎች አማከሩ፡፡

በሌላ በኩል የኮሚኒስቷ ሶቪየት ህብረት በጦርነቱ በአሸናፊነት መውጣት ለመስፋፋት የልብ ልብ እንዳይሰጣት ለማስጠንቀቅም ነው ተብሏል፡፡

ስለዚህ፣ አዲሱን ቦምብ ተጠቅሞ ጦርነቱን ቶሎ የማጠናቀቁን አስፈላጊነት ትሩማን አመኑበት፡፡
ሐምሌ 29/1937 15 ሺህ ቶን ክብደት ያለውና ትንሹ ልጅ ብለው የሰየሙትን አቶሚክ ቦንብ በሂሮሽማ ላይ አዘነበች፡፡

ይህ ማለት የማጥፋት አቅሙ 15 ሚሊዮን ኪግ ከሚመዝኑ ቦምቦች የሚበልጥ ነበር፡፡
ቦምቡ የሂሮሽማን ከተማ በአምስት ስኳየር ኪሎ ሜትር ስፋት፣ ምልክት ሳይተው እንዳልነበረች አድርጎ አወደማት፡፡

ከሶስት ቀናት በኋላ፣ በሌላዋ የጃፓን የወደብ ከተማዋ ናጋሳኪ ላይ፣ አሜሪካ ተመሳሳይ የአቶሚክ ቦምብ ጣለች፡፡

40 ሺህ የሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች በሰኮንዶች ውስጥ ፀጥ አሉ፡፡

የአቶሚክ ቦምብ ናዳ የወረደበት የጃፓን መንግስት፣ ያለምንም አስገዳጅ ጥያቄ እጁን ሰጠ፡፡
በጃፓን የደረሰው የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የሁለተኛው የአለም ጦርነት አስቁሟል ፡፡
ግን ፣አለም ሰላም ያጣችበት የቀዝቃዛው ጦርነት መጀመሪያ ሆነ፡፡

ነግ በኔ ያለችው ሶቪየት ህብረት ፣ ቀመሩን ከአሜሪካ አስርቃ የኒዮክለር ቦምብ ባለቤት ሆነች፡፡
ሌሎች ሃገሮች ፈለጉን ስለተከተሉ ፣ አለም በቅራኔ ውስጥ ባሉ ሃገሮች ፍጥጫ በኒዩክለር ቦምብ ስጋት ላይ ወደቀች፡፡

አሜሪካ በሂሮሺማ ላይ የአቶሚክ ቦምብ ጥላ ህዝቡን ከፈጀች ዛሬ 90 ዓመት ሆነ፡፡

እሸቴ አሰፋ

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

📌 Telegram; t.me/ShegerFMRadio102_1

📌 YouTube: shorturl.at/P4mpX

📌 WhatsApp: tinyu.com/ycxjmm3s

112 - 1

Sheger FM 102.1 Radio
Posted 4 weeks ago

ታሪክን የኋሊት

ሐምሌ 22 2017

ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ፣ በፋሽስት ጣሊያን ሰማዕትነት የተቀበሉት 89ኛ አመት ዛሬ ይታሰባል፡፡

ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ፣ መስቀልና ወንጌል ብቻ ይዘው የወራሪውን የኢጣሊያ ፋሽስት ፣ ነውሩንና ግፉን ፊት ለፊት ታግለው፣ ለሃገራቸውና ለሃይማኖታቸው ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡት ፣ በ1928 በዛሬው ቀን ነበር፡፡

አባ ኃይለማርያም፣ ከመጀመሪያዎቹ አራት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት አንዱ ሆነው ሲመረጡ ስማቸው ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ሆነ፡፡

በቅኔ ፣ በዜማ ፣ በመፃህፍት ትርጓሜ የተመረቁት አቡነ ጴጥሮስ፣ በ1921 ዓ.ም ጳጳስነት ከተሾሙ በኋላ፣ የኢጣሊያ ወረራ እስከገፋበት ድረስ ወሎንና ከሸዋ መንዝን እና ኤፍራታን፣ ግሺና አንጾኪያን ሃገረ ስብከታቸው አድርገው ቆይተዋል፡፡

ከዚያ በፊትም በወላይታና በዝዋይ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

በማይጨው ዘመቻ ጊዜ ፣ ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ሳይለዩ በማይጨው ተዋጊውን ሰራዊት እያበረታቱ አዋግተዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያኑ ድል ሆነው ሲያፈገፈጉ በትውልድ አካባቢያቸው በሰላሌ ከተሰማሩት አርበኞች ከነዳጃዝማች አበራ ካሣ ጋር ተቀላቅለው ቆዩ፡፡

በ1928 ሐምሌ ወር አዲስ አበባን ከኢጣሊያኖች ለማስለቀቅ በተደረገው ከበባ በሰሜን በኩል ከዘመቱት አርበኞች ጋር አዲስ አበባ ደረሱ፡፡

አርበኞች አልቀናቸውም፡፡ ድል ሆነው ሲመለሱ ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ግን ለመመለስ አልፈለጉም፡፡

ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ፀሎት አድርገው በቀጥታ ወደመሐል ከተማ ገብተው ተያዙ፡፡

የኢጣሊያ ሹማምንት ፣ አቡነ ጴጥሮስን አባበሉዋቸው፡፡

የኢጣሊያን ገዥነት ካመኑ በክብር እንደሚያዙ ነገሩዋቸው፡፡

ጳጳሱ ግን እምቢ አሉ፡፡

ገንዘብህ ለጥፋትህ ይሁን ብለው ረገሙ፡፡

እንኳንስ ሰው፣ ምድሩዋ እንዳትገዛ አወገዙ፡፡

በአቡነ ጴጥሮስ ድርጊት የተናደደው ጀኔራል ግራዚያኒ ፣ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡

ሐምሌ 22-1928 ዓ.ም ፣ ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ፣ በሰንሰለት ታስረው ፣ ከአራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በስተምዕራብ ባለው ቦታ ቆሙ፡፡

ከኋላቸው 8 ወታደሮች ጠመንጃቸውን ወድረው ተሰልፈዋል፡፡

በጊዜው በቦታው የነበረው ጋዜጠኛ እንደፃፈው ጥቁሩ ቀሚሳቸው ጭቃ ነክቶታል፡፡
ወንጌላቸውንና መስቀላቸውን ይዘዋል፡፡

ግድያቸውን እንዲመለከት በትዕዛዝ የተሰበሰበው ሕዝቡም ሆነ ምድሩዋ እንዳትገዛላት አወገዙ፡፡
ከረፋዱ 5፡30 ሆኖ ነበር፡- ይልና ጋዜጠኛው ስላሟሟታቸው እንዲህ ይላል፡፡

“አንድ መኮንን ውሳኔውን እየተንቀጠቀጠ ሲያነብ ፣ እሳቸው ግን ያለምንም ስጋት ያዳምጡት ነበር፡፡

ወዲያው ዓይንዎ እንዲሸፈን ይፈልጋሉ ሲል ጠየቃቸው፡፡ “እሱ የናንተ ተግባር ነው” አሉት፡፡
ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ወታደሮቹ ተኮሱ፡፡

በስምንት ጥይትም መቷቸው ግን አልሞቱም ነበርና ፣ ኮሎኔሉ በሶስት የሽጉጥ ጥይት፣ ራስ ቅላቸው ላይ ተኩሶ ገደላቸው፡፡ ሕዝቡም በሀዘን ተመታ ይላል፡፡

ጋዜጠኛው ፣ ንብረታቸውን ወስደሁ ያለው ወታደር እንደነገረው ፣ ወንጌላቸውና መስቀላቸው በጥይት ተበሳስቷል፡፡

አቡነ ጴጥሮስ በ53 ፣ አመታቸው ፣አሁን ሐውልታቸው በቆመበት አካባቢ ተገድለው ባልታወቀ ቦታ ተቀብረዋል፡፡

ከነፃነት በኋላ በ1938 ለመታሰቢያ እንዲሆን ሐውልት ተቀርፆ ቆመላቸው፡፡

አሁን ያለው ሐውልት ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ ተቀርፆ የቆመላቸው ነው፡፡
በፍቼም ለሶስተኛ ጊዜ ሐውልት ተቀርፆላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ድምፅ በወሰነው መሰረት ፣ ሰማዕትነታቸውን አፅድቆ በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶላቸዋል፡፡

ሰማዕተ ፅድቅ አቡነ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ፣ የታነፀው በትውልድ ቀያቸው በፍቼ ነው፡፡

የብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የብዙ የጥበብ ሰዎችን ስሜት እየገዛ ገጣሚዎች ገጥመውላቸዋል፣ ቅኔ አዋቂዎች ቅኔ ዘርፈውላቸዋል ፣ ድራማ ተሰርቶላቸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስቶች ከተገደሉ 89 ዓመት ሆነ፡፡

እሸቴ አሰፋ

https://youtu.be/T4kGOTj7C8c

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

📌 Telegram; t.me/ShegerFMRadio102_1

📌 YouTube: shorturl.at/P4mpX

📌 WhatsApp: tinyurl.com/ycxjmm3s

761 - 13